ሕገ ደንብ / Statute

 

በአየርላንድ የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ
ሕገ ደንብ
ጥር 2008 ዓ.ም

 

 

መግቢያ

`      በአየርላንድ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ከትውልድ አገራችን ርቀን በመኖር የሚያጋጥሙንን የተለያዩ ችግሮች በጋራ ለመቅረፍና አገራችን ኢትዮጵያንም ለማስተዋወቅ በአየርላንድ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አቋቁመናል።ማህበረሰቡ ከምንኖርበት አገር ባህል ህግና የኑሮ ዘይቤ ጋር በማጣጣምና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚያግዘን ሲሆን ከማንኛውም የዘር፤የፖለቲካና የሃይማኖት ዓላማ የጸዳ ነው።አገራችን ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሌሎች አገሮች በተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች የበለጸገች ናት።አገራችን በታሪክ በዓለም ላይ ካሉት ቀደም ያለ ታሪክ ካላቸው አገሮች ውስጥ የምትሰለፍ በመሆኗና፤ ይህንንም የማስተዋወቅና የመጠበቅ የውዴታ ግዴታም ስላለብን ይህንን ማህበረሰብ መስርተናል።

አንቀጽ 1 ስያሜ

1 1 የማህበረሰቡ መጠሪያ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በአየርላንድ ተብሎ ይጠራል።

አንቀጽ 2 የደንቡ ተፈጻሚነት ወሰን

2 1 ይህ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ደንብ በመላ አየርላንድ በሚኖሩ የማህበረሰቡ አባላት ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

አንቀጽ 3 አድራሻ

3 1 የማህበረሰቡ ዋና ጽህፈት ቤት በአየርላንድ ዋና ከተማ በደብሊን ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች ከተሞች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሊኖረው ይችላል።

አንቀጽ 4 ትርጓሜ

በዚህ የመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ፦

4 1 ኢትዮጵያዊ ማለት በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑትንና በአየርላንድ የተወለዱትን ኢትዮጵያውያንን ይጨምራል።

4 2 አየርላንድና አካባቢው ማለት በአየርላንድ ውስጥ ሆኖ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩትን አባላት ይመለከታል።

4 3 አባል ማለት የአባልነት መመዘኛውን በሟሟላት ግዴታውንም በአግባቡ የሚወጣ ሰው ሲሆን ይህም በሁሉም የስራ ሃላፊነት ተመርጠው የሚያገለግሉትንም ያጠቃልላል።

4 4 በንዑስ አንቀጽ 4 1 3 ላይ እንደተጠቀሰው ሆኖ አባል የሚለው ፍቺ የሚወክለው ሁለቱንም ፆታዎች ነው።

4 5 ቤተሰብ ማለት የአባሉ ወይም የአባሏ የትዳር ጓደኛና ልጅ ማለት ነው።

4 6 ማህበረሰብ ማለት የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በአየርላንድ ማለት ነው።

4 7 ጠቅላላ ጉባኤ ማለት የአባልነት መመዘኛውንና ግዴታቸውን የተወጡ መላውን አባላት የሚያካትት ሲሆን የማህበረሰቡ የመጨረሻ ወሳኝ አካል ማለት ነው።

4 8 ቦርዱ ማለት ከማህበረሰቡ ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጠና ማህበረሰቡንም በበላይነት የሚመራ ማለት ነው።

4 9 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማለት በጠቅላላ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ የሚመረጡና የማህበረሰቡን የየዕለት ተግባራት የሚከታተል ነው።

4 10 ሊቀ መንበር ማለት በጠቅላላ ጉባኤ የሚመረጥ የስራ አስፈጻሚውን ኮሚቴ በሃላፊነት የሚመራና ማህበረሰቡን የሚወክል ማለት ነው።

አንቀጽ 5 የማህበረሰቡ ዓላማ

5 1 የመተሳሰብ፤የመተባበርና በፍቅር አብሮ የመኖርን ባህል ለማዳበር እንዲሁም በግል ወይም በጋራ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጋራ ለመቋቋም እንድንችል፤

5 2 በሞት፤በህመም፤በአደጋ፤በስራ ማጣት፤ወዘተ የኢኮኖሚ ችግር ለሚያጋጥማቸው የማህበረሰቡ አባላት ምክር ድጋፍና ዕርዳታ ለማድረግ፤

5 3 በአየርላንድ የሚኖሩና አዲስ የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን በኢኮኖሚ፤በማህበራዊ ኑሮ፤በስራ፤በትምህርትና በሌሎች ጠቃሚ መስኮች የሚረዱበትን መንገድ እያጠና ተግባራዊ ለማደረግ፤

5 4 የኢትዮጵያን የተለያዩ ባህሎች፤ ወጎች፤ቅርሶች ለማስተዋወቅና ለመጠበቅ፤

5 5 ከኢትዮጵያውያን ወላጆች የተወለዱ ልጆችና በማደጎ ወደዚህ አገር መጥተው የሚኖሩ ህጻናት አገራቸውን ኢትዮጵያን እንዲያውቁ፤እንዲያፈቅሩ ፤ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲያስታውሱ እንዲማሩና እንዲያዳብሩ ለማድረግ፤

5 6 በአየርላንድ ካሉ ተመሳሳይ ይዘትና ዓላማ ካላቸው የሌሎች አገሮች ማህበራትና ድርጅቶች ጋር የስራና የደብዳቤ ግንኙነት በመፍጠር ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር እኩል ተሳታፊና ገንቢ ህብረተሰብ እንዲሆኑ ለመጣር፤

5 7 በኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ ከኢትዮጵያም ውጪ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ለሚደርሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወይም ችግሮች ፤የሰብዓዊ መብቶች መጣስ ለኢምግሬሽን ጉዳዮች መፍትሄ ለመፈለግና ሲቻልም ሰብዓዊ፤ሞራላዊና ማቴርያላዊ ዕርዳታ ለማድረግ፤

5 8 ወደ አየርላንድ የመጡ አዲስ ነዋሪዎችን በማህበረሰቡ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለመርዳት፤

አንቀጽ 6 አባልነት

የማህበረሰቡ አባል ለመሆን ከዚህ በታች የተጠቀሱትን የሚያሟላ አባል መሆን ይችላል።

6 1 ኢትዮጵያዊ የሆነ፤

6 2 ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ፤

6 3 የማህበረሰቡን መተዳደሪያ ደንብ የተቀበለ፤ የአባልነት ማመልከቻ የሞላ

6 4 በአየርላንድ ነዋሪ የሆነና ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ያለው ወይም ኢትዮጵያዊ የሆነን ሰው ምስክር ማቅረብ የሚችል መሆን አለበት፤

አንቀጽ 7 የአባልነት ግዴታዎች

7 1 ማንኛውም አባል ቦርዱ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ የማድረግ፤

7 2 ማንኛውም አባል የማህበረሰቡን ህግና ደንብ የማክበር፤የመጠበቅ ዓላማዎቹንና የመፈጸምና የማስፈጸም ሃላፊነት አለበት።

7 3 ማንኛውም አባል ማህበረሰቡ በሚጠይቀው የስራ ድርሻ የመሳተፍ የውዴታ ግዴታ አለበት።

7 4 ማንኛውም አባል ተመርጦ የማገልገል ሃላፊነት አለበት።

7 5 ማንኛውም አባል የመምረጥም የመመረጥም ሃላፊነትና ግዴታዎች አሉበት።

7 6 በአባላት መካከል የመግባባትና የመተባበር ስሜት እንዲዳብር ምሳሌ የመሆን ግዴታ አለበት።

7 7 የአባል ቤተሰብ ላይ በሚደርስ ሃዘን በአካል በመገኘት የማስተዛዘን ግዴታ አለበት።

አንቀጽ 8 የአባላት ጥቅሞች

8 1 እያንዳንዱ አባል ማህበረሰቡን ለማጠናከር ለማጎልበትና ለማሳደግ የአቅሙንና የችሎታውን አስተዋጽዖ ማድረግ መብቱም ግዴታውም እንደሆነው ሁሉ ከማኀበረሰቡ የሚገኝንም ጥቅም በእኩልነት የመካፈል መብት አለው።

8 2 የማኀበረሰቡ አባላት ማኀበረሰቡ በሚያካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚያስገኙ የተለያዩ ስራዎች በሚፈጠሩ ጊዜ አባላት መሳተፍ ይችላሉ።ስራውን ለማግኘት ከአንድ በላይ አመልካችች ከቀረበ ግን ቦርዱ ከተወዳዳሪዎቹ ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ ወይም በማወዳደር ይወስናል።

8 3 ማንኛውም አባል የሆነ ጋብቻ ሲፈጽም ለአንድ ጊዜ 250/ሁለት መቶ ሃምሳ/ ዩሮ ስጦታ ይደረግለታል።

8 3 1 የማኀበረሰቡ አባላት የሆኑ እርስ በርስ ጋብቻ ቢፈጽሙ ክፍያ የሚደረገው እንደ አንድ አባል ተደርገው ይሆናል።

8 4 የማህበረሰቡ አባል በሞት ከተለየ ለተጠሪው አካል 1000/አንድ ሺ/ ዩሮ ይሰጣል።

8 5 – ከአባል ቤተሰብ ጋር አብረው በሚኖሩ የቤተሰብ አባል ላይ የሞት አደጋ ቢደርስ ለወጪ መሸፈኛ 500/ አምስት መቶ ዩሮ ይሰጣል።እንዲሁም እዛው ቤተሰብ ውስጥ በእንግድነት የመጣ ቢኖርና የሞት አደጋ ቢደርስበት ክፍያው እንደ አንድ ቤተሰብ ተቀጥሮ 500/አምስት መቶ/ ዩሮ ይሆናል።

8 6 በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለትና ከሁለት በላይ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው በቤተሰቡ ውስጥ ቢኖሩ ክፍያ የሚደረገው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

8 7 ማንኛውም የጋብቻ ወይም የሃዘን ክፍያ የሚፈጸመው ማኀበረሰቡ ከተመሰረተ ከአንድ ዓመት በኋላ ሆኖ፤ ወጪ የሚያስፈልግ ሁኔታ ሲያጋጥም በማንኛውም ጊዜ ይጀምራል።

8 8 የማህበረሰቡ አባል የመታሰር ዕድል ቢገጥመው በአየርላንድ ሕግ መሰረት አቅሙ በፈቀደ መንገድ የማኀበረሰቡን ደንብ ተመርኩዞ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኝ ያደርጋል።

8 –9 የማህበረሰቡ አባል የሆነ አባልነቱን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲጻፍለት የፈለገ እንደሆነ መብትና ግዴታዎቹን በአግባቡ የፈጸመ መሆኑን ተመልክቶ የጠየቀውን ይፈጽምለታል።

አንቀጽ 9 የአባልነት ክፍያ

9 1 የማህበረሰቡ የአባልነት ክፍያ በግለሰብ በወር 5/ አምስት/ ዩሮ ነው።

9 2 ማህበረሰቡ ከተመሰረተ ከአንድ ዓመት በኋላ አዲስ የሚገቡ የማህበረሰብ የአባልነት ክፍያ ለመመዝገቢያ 20/ሃያ/ ዩሮ ይሆንና በተጨማሪም ወርሃዊውን ክፍያ 5 /አምስት/ ዩሮ ይከፍላል።

9 3 ማንኛውም ነባር አባል ሆነ አዲስ ገቢ ተጨማሪ መዋጮ መክፈል ይችላል።

አንቀጽ 10 የክብር አባልነት

10 1 በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ያልሆነና የማህበረሰቡን ደንቦችና መመሪያዎች ለመፈጸም የሚችል አየርላንዳዊ የክብር አባል መሆን ይችላል።

10 2 የማህበረሰቡ የክብር አባል በደብዳቤ ጥሪ ካልተደረገለት በስተቀር በማህበረሰቡ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ መገኘት አይችልም።

10 3 የማህበረሰቡ የክብር አባል ከማህበረሰቡ ቦርድ ጋር በመነጋገር ለማህበረሰቡ የተለያዩ እገዛዎችን ያደርጋል።

አንቀጽ 11 ከማህበረሰቡ ስለመሰናበት

11 1 ማንኛውም የማህበረሰብ አባል በማንኛውም ጊዜ በራሱ ፈቃድ የማህበረሰብ አባልነቱን ማቆም ይችላል። ከማህበረሰቡም የሚለቅበትን ምክንያት ገልጾ ደብዳቤ ሲጽፍ ከማህበረሰቡ የምስክር ወረቀት ማግኘት ይችላል።

11 2 የአባልነት ክፍያን በተከታታይ ለአራት ወራት ያልከፈለ ግዴታውን አለመወጣቱን ተነግሮት ይሰናበታል።

11 3 ከአንድ ዓመት በላይ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነቱን ሲያቋርጥ ይሰናበታል።

11 4 አየርላንድን በቋሚነት ለቆ ሲሄድ ይሰናበታል።

11 5 ከማህበረሰቡ የለቀቀ አባል የከፈለው ገንዘብ አይመለስለትም።

አንቀጽ 12 ከማህበረሰቡ የሚያሰናብቱ አስገዳጅ ሁኔታዎች

12 1 ከማህበረሰቡ ዓላማዎች ውጪ ማህበረሰቡን የሚጎዳና የሚያዳክም ፤

12 2 በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ አባላትንና የአባላትን ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት የሚፈጽም፤

12 3 አሉባልታ የሚነዛ፤ቡድንተኛ የሆነ፤የመበተንና ከፋፋይ ወሬዎችን የሚያወራ፤

12 4 ከማህበረሰቡ ዓላማ በተቃራኒ የቆመ፤

12 5 የአባልነት ግዴታዎችን ከሶስት ተከታታይ ጊዜ በላይ ማከናወን ከተሳነውና ለሌሎች መጥፎ አርአያ ከሆነ ይወገዳል፤

አንቀጽ 13 ወደ ማህበረሰቡ ተመልሶ ስለ መግባት

13 1 ከማህበረሰቡ አባልነት የለቀቀ ወደ ማህበረሰቡ ተመልሶ መግባት የፈለገ እንደሆነ ምክንያቱን ገልጾ ማመልከቻ ደብዳቤ ማቅረብ አለበት። እንዲመለስ ከተወሰነለት በኋላ ቅጣት 30/ ሰላሳ/ ዩሮ ከፍሎና ያልከፈለው ውዝፍ ካለበት ከፍሎ ይመለሳል ።

13 2 ከማህበረሰቡ የተሰናበተው በዲስፕሊን ጥፋት ከሆነ የሚጽፈው ደብዳቤ ይቅርታ እንዲደረግለት የሚገልጽ መሆን አለበት።

13 3 ለሁለተኛ ጊዜ ከማህበረሰቡ ከተሰናበተ በምንም መንገድ ወደ ማህበረሰቡ መመለስ አይችልም።

አንቀጽ 14 የገቢ ምንጮች

14 1 ከአባልነት የሚገኝ መመዝገቢያና መዋጮ፤

14 2 የተለያዩ ገቢ ማግኛ መንገዶችን በመፈለግ፤ ዝግጅቶችን በማድረግ፤ ዓመታዊ በዓላትን በማክበር፤

14 3 የፕሮጀክት ሃሳቦችን፤ፕሮጀክቶችን የመቅረጽ በማመንጨትና መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ዕርዳታ በመጠየቅ፤

አንቀጽ 15 ጠቅላላ ጉባዔ

15 1 የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በአየርላንድ ዓላማ ለማራመድ የአባልነት ግዴታዎችን የሚወጡ አባላትን በሙሉ ያካተተ ስብስብ ሲሆን ፤የሚከተሉት ዓላማዎችና ተግባሮች ይኖሩታል።

15 1. 1 ወሳኝ የሆኑና በደንቡ ላይ የተመለከቱትን የማህበረሰቡን ጉዳዮች የመወሰኛ የመጨረሻው አካል ነው።

15 1. 2 የስራ አስፈጻሚ፤የቁጥጥር ኮሚቴ አባላትንና የቦርድ አባላትን ይመርጣል።

15 1. 3 ከየኮሚቴዎቹ የሚቀርቡለትን የስራ አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርቶች አዳምጦ ውሳኔ ያሳልፋል።

15 1. 4 የቦርዱ ሰብሳቢ ጠቅላላ ጉባዔ ከጠራ ይሰበሰባል።

15 1. 5 የተጓደሉ የስራ ቦታዎች ካሉ በምትኩ ሌላ መርጦ ይሾማል።

15 1. 6 ዓመታዊ በጀት ያጸድቃል፤አፈጻጸሙም ህግና ደንብ የተከተለ መሆኑን ያረጋግጣል።

15 1. 7 የመተዳደሪያ ደንቡን ያጸድቃል፤አስፈላጊ ሲሆን ያሻሽላል።

15 1 8. ከማህበረሰቡ አባላት ከግማሽ በላይ ከሆነ ምልዓተ ጉባዔ ይሆናል።

15- 1. 9 ምልዓተ ጉባዔ በመጀመሪያው ስብሰባ ላይ ካልተገኘ በሁለተኛው ስብሰባ ዕለቱ የተገኙት ከ 75% በላይ ስብሰባ እንዲቀጥል ከተስማሙ ጉባዔ ማካሄድ ይችላሉ።

አንቀጽ 16 ቦርድ

የቦርዱ ሰብሳቢ ተወክለውና በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠው በተሰበሰቡት የቦርድ አባላት የሚመረጥ ሲሆን ተጠሪነቱ ለማህበረሰቡ ጠቅላላ ጉባዔ ይሆናል።

16 1 አምስት አባላት ይኖሩታል።

16 2 ኢትዮጵያዊ የሆነ አንድ ፕሬዝዳንትና አንድ ጸሃፊ ይኖሩታል።

16 3 የቦርዱ ፕሬዝዳንት በጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጥ ይሆናል።

16 4 የስራ አስፈጻሚው ሰብሳቢ የቦርዱ ጸሃፊ ይሆናል።

16 5 የሌሎች የቦርዱ አባላት የስራ ድርሻ በቦርዱ የሚወሰን ይሆናል።

16 6 በጠቅላላ ጉባዔው ከሚመረጡት የቦርድ አባላት ውስጥ 1/3ኛው በየሁለት ዓመቱ በአዲስ ይተካሉ።

አንቀጽ 17 የቦርዱ ተግባር

17 1 ለጠቅላላ ጉባዔው ተጠሪ በመሆን ማህበረሰቡ የተቋቋመለትን ዓላማና ተግባር ከግብ ለማድረስ ኃላፊነት የተሰጠው የማህበረሰቡ የበላይ ጠባቂና አስተዳዳሪ ወይም መሪ አካል ነው።

17 2 የማህበረሰቡ ህጎችና ደንቦች በስራ አስፈጻሚው በትክክል መተርጎማቸውንና መፈጸማቸውን በበላይነት ይቆጣጠራል።

17 3 ስራቸውን በብቃት ለመወጣት ያልቻሉ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ጉዳይ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጉዳዩን ለጠቅላላ ጉባዔ አቅርቦ ያስወስናል።

17 4 የማህበረሰቡ የመተዳደሪያ ደንቦች እንዲሁም ዓላማዎቹ እንዲዳብሩና ጥልቀት እንዲያገኙ አዳዲስ የማሻሻያ ሃሳቦችን እያጠና ለጠቅላላ ጉባዔ ያቀርባል።

17 5 ስራ አስፈጻሚው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች፤ማህበራትና ድርጅቶች ጋር የሚፈጥረው ግንኙነት ከዘር፤ከፆታ፤ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ መሆኑን ይቆጣጠራል።

17 6 በማህበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ማንኛውንም አለመግባባቶች የስልጣን ተዋረዱን ጠብቆ ሲቀርብለት የማህበረሰቡን የመተዳደሪያ ደንብና መንፈስ በመመርኮዝ መፍትሄና መመሪያ ይሰጣል።

17 7 የማህበረሰቡን ዓርማ ወይም መታወቂያዎች ፤ፎርሞች፤ቅጾችና የስራ ሰነዶች /ለምሳሌ መጽሄቶች፤ድረ ገጾች / ስሞች የማህበረሰቡን ሁለንተናዊነት የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑና ተጠንተው እንዲዘጋጁ ያደርጋል።አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም በስራ አስፈጻሚው እንዲጸድቁ ያደርጋል።

17 8 በስራ አስፈጻሚው የሚቀርበውን አጠቃላይ የስራ ሪፖርት ተመልክቶ ለጠቅላላ ጉባዔው እንዲቀርብ ያደርጋል።

17 9 በየሶስት ወሩ በመሰብሰብ የማህበረሰቡን የስራ አስፈጻሚ እንቅስቃሴ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያደምጣል፤እርማት ይሰጣል፤ያጸድቃል።አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም ተጨማሪ ስብሰባዎችን መጥራት ይችላል።

17 10 የቦርዱ አባላት ቦርዱ የተቋቋመበትን ዓላማ ይቆጣጠራል፤የሚጠበቅባቸውን ክፍያ መክፈላቸውን ፤ንቁ ተሳታፊ መሆናቸውን ይከታተላል።

አንቀጽ 18 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

18 1 ዘጠኝ አባላት ያሉት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጠቅላላ ጉባዔ ይመረጣል።

18 2 የስራ ዘመኑ ሶስት ዓመት ይሆናል።

18 3 ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔውና ለቦርዱ ይሆናል።

18 4 የማህበረሰቡን የዕለት በዕለት ስራ ይመራል።

18 5 ለመጀመሪያው የስራ ዓመት የማህበረሰቡን እንቅስቃሴ በየአራት ወሩ የስራ ሪፖርቱን ለቦርዱ ያቀርባል።

18 6 የማህበረሰቡን ዓመታዊ ዕቅድና በጀት አውጥቶ ለቦርዱ ያቀርባል፤ሲጸድቅለትም ስራ ላይ ያውላል።

18 7 እንደ አስፈላጊነቱ ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን ያዋቅራል ፤ምክንያቱንም ገልጾ ለቦርዱ ደብዳቤ ይጽፋል።

18 8 ሊቀ መንበር ፤ምክትል ሊቀ መንበር ፤ጸሃፊ፤ ገንዘብ ያዥ፤ ሂሳብና ፋይናንስ፤የውስጥ ኦዲተር፤የህዝብ ግንኙነት፤የባህልና ስፖርት፤ሴቶች ወጣቶችና ህጻናትን የሚወክሉ ይኖሩታል።

አንቀጽ 19 የማህበረሰቡ ሊቀ መንበር

19 1 የቦርዱ ጸሃፊ ይሆናል።

19 2 የማህበረሰቡን የዕለት በዕለት ስራ ይመራል።

19 3 ከቦርዱ የቀረበለትን ዓመታዊ ዕቅድና በጀትያስፈጽማል።

19 4 ከሒሳብ ሹም ኃላፊ ጋር በመሆን ቼኮችን ይፈርማል።

19 5 ለማህበረሰቡ ለሚጻፉ ደብዳቤዎች መልስ ይጽፋል፤በየስድስት ወሩ ለቦርዱ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀርባል።

19 6 ስራቸውን በትክክልና በብቃት መወጣት ላልቻሉ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሲኖሩ ለቦርዱ በማቅረብ አስፈላጊውን ውሳኔ ያስወስናል።

19 7 ጠቅላላ ጉባዔውና ቦርዱ የሚሰጠውን ስራዎች አቀናብሮ ይመራል።

19 8 በስሩ ያሉት ኮሚቴዎችን በጥብቅ ይቆጣጠራል።

አንቀጽ 20 የማህበረሰቡ ም/ ሊቀ መንበር

20 1 የማህበረሰቡ ሊቀ መንበር በሌለበት ወቅት ሊቀ መንበሩን በመተካት ከላይ በአንቀጽ 20 የተጠቀሱትን ያከናውናል።

20 2 ሊቀ መንበሩ በችግር ወይም በሌላ ምክንያት ስራውን መቀጠል ባይችል ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ሌላ እስኪመረጥ ድረስ የስራ አስፈጻሚውን ኮሚቴ ይመራል፤የቦርዱ ጸሃፊም ሆኖ ያገለግላል።

20 3 በስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ስር የሚዋቀሩትን ንዑሳን ኮሚቴዎች ይመራል።

20 4 ከፖለቲካ ወገናዊነት ነጻ በሆነ መንገድ በኢትዮጵያ የሚደረጉ ግልጽ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን ይከታተላል፤ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ያቀርባል።ሪፖርቱን ለቦርዱ አቅርቦ ካስጸደቀ በኋላ በማህበረሰቡ ስም የአቋም መግለጫዎችን ያወጣል።

አንቀጽ 21 የማህበረሰቡ ጸሃፊ

21 1 የስራ አስፈጻሚውን ኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳዎች ከሊቀ መንበሩ ጋር በመመካከር ያዘጋጃል፤የስብሰባ ቃለ ጉባዔ ይይዛል።

21 2 የማህበሩን ዶክመንቶችንና ማህተሞችን ይይዛል

21 3 የማህበረሰቡን የዕለት በዕለት የጽህፈት ስራ ይመራል፤ለማህበረሰቡ የተላኩ ደብዳቤዎች ወቅታዊ ምላሽ እንዲያገኙ አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል።

21 4 ከስራ አስፈጻሚው የተወሰኑትን ውሳኔዎች ለአባላት ያስተላልፋል።

21 5 ሊቀ መንበሩና ም/ ሊቀ መንበሩ በሌሉበት ጊዜ የስራ አስፈጻሚውን ስብሰባ ይመራል፤ሊቀ መንበሩና ም/ ሊቀ መንበሩ ስራቸውን መቀጠል ባይችሉ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ተተኪዎች እስኪመረጡ ድረስ የስራ አስፈጻሚውን ኮሚቴውን ስራ ይመራል።

21 6 የአባላትን የስም ዝርዝርና ወቅታዊ የሆነ ሙሉ መረጃ ይይዛል።አባላትን የተመለከተ የግል መረጃዎች ከጉዳዩ ባለቤት ውጪ ያለፈቃዳቸው በምንም መንገድ ከማህበረሰቡ ውጪ ላሉ ግለሰቦች እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል።

21- 7 የስራ አስፈጻሚውን ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ይይዛል።

አንቀጽ 22 የሂሳብ ሹም

22 1 ከስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጋር በመመካከር የማህበረሰቡን በጀት ያዘጋጃል፤በንዑሳን ኮሚቴዎች የሚቀርቡለትን ዓመታዊ በጀቶች ከአጠቃላይ የማህበረሰቡ በጀት ጋር ያመሳክራል፤ከሊቀ መንበሩ ጋር በመሆን የማህበረሰቡን አጠቃላይ በጀት ለቦርዱ ያቀርባል።

22 2 በቦርዱ የጸደቀው በጀት በትክክል ስራ ላይ መዋሉን ይከታተላል።

22 3 ከገንዘብ ያዢ/ ንብረት ሃላፊና ከውስጥ ኦዲት ኮሚቴ ጋር በመሆን የማህበረሰቡን የሂሳብና የንብረት ቅጾች ያዘጋጃል።

22 4 ከገንዘብ ያዢ/ ንብረት ሃላፊ / የወጪ ዝርዝሮችን ወቅታዊ በሆነ መንገድ በመሰብሰብ የገቢና ወጪ ዘገባን በየስድስት ወሩ በማዘጋጀት ለስራ አስፈጻሚውን ኮሚቴ ያቀርባል።

22 5 የማህበረሰቡን የታክስ ፋይል ያዘጋጃል።

22 6 ሊቀ መንበሩ ወይም ምክትል ሊቀ መንበሩ በሌሉበት ጊዜ ሒሳብ ሹሙ ቼክ ላይ ይፈርማል።

አንቀጽ 23 ገንዘብ ያዥ/ንብረት ሃላፊ/

23 1 በዘመናዊ የገንዘብና የንብረት አያያዝ ዘዴ የማህበረሰቡን ገንዘብ፤ንብረት ይይዛል፤ይቆጣጠራል።ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ያደርጋል።

23 2 የአባልነት መመዝገቢያና ዓመታዊ ክፍያን ይሰበስባል፤ህጋዊ ደረሰኝም ይሰጣል።

23 3 ማንኛውም ገቢና ወጪ ሃላፊነትና ስልጣን በተሰጠው አካል አማካኝነት እንዲፈጸም ያደርጋል።

23 4 ገንዘብ ያዡ የማኀበሩን ቼክ ይይዛል።

23 5 ለዕለት ተዕለት ተግባሮች የሚያስፈልጉትን የጽህፈትና ሌሎች ቁሳቁሶች ያቀርባል፤ይቆጣጠራል፤ለጥቃቅን ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ ይይዛል።

23 6 ለእያንዳንዱ ወጪና ገቢ ደረሰኝ ግልባጩን ለሂሳብ ሹሙ ያስረክባል።

23 7 በሊቀ መንበሩ የሚሰጡትን ተግባሮች በመተባበር ያከናውናል።

አንቀጽ 24 የውስጥ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ

24 1 በጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጡ ሶስት የሂሳብና የንብረትና አስተዳደር ሙያተኞች ያቀፈ ሲሆን ዝርዝር ተግባርና ሃላፊነቱም፦

24 1.1 የማህበረሰቡን የገንዘብ የሂሳብና የንብረት አያያዝ ደንብ በማዘጋጀት በቦርዱ ሲጸድቅ ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ያስተላልፋል።

24 -1.2 በአመት አንድ ጊዜ ዝርዝር የኦዲት ሪፖርት ለቦርዱ፤ለስራ አስፈጻሚውና ለጠቅላላ ጉባዔ ያቀርባል።

24 -1.3 እንደ አስፈላጊነቱ በማንኛውም የስራ ጊዜ የገንዘብ ሆነ የስራ አፈጻጸም ምርመራና ኦዲት በማድረግ ለቦርዱ ወይም ለጠቅላላ ጉባዔ ያቀርባል።

24 -1.4 የስራ ዘመን ከመጠናቀቁ ከ2 ወር በፊት ዝርዝር የኦዲት ሪፖርት ያዘጋጃል፤የርክክብ ሰነድ በማዘጋጀት አዲስ ተመራጮችና ነባሮች እንዲፈራረሙ ያደርጋል።

24 -1.5 ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባዔ ይሆናል።

አንቀጽ 25 የህዝብ ግንኙነት

25 1 የማህበረሰቡን ዓላማና የስራ እንቅስቃሴ ለመገናኛ ብዙሃን ያሰራጫል።

25 2 የማህበረሰቡን ድረ ገጽ ያስተዳድራል፤ወቅታዊ መረጃዎችን ያስቀምጣል።

25 3 የጠቅላላ ጉባዔውን ፤የቦርዱን፤የስራ አስፈጻሚውን ስብሰባ በቪድዮ በመቅረጽ ፋይል ያደርጋል።

25 4 የየኮሚቴዎችን ዓብይ የስራ እንቅስቃሴዎች በድምጽና በምስል በመቅረጽ ለህብረተሰቡ ያደርሳል።

25 5 የማህበረሰቡን እንቅስቃሴ የሚያሳይ መጽሄት ወይም በራሪ ወረቀት በየስድስት ወሩ አዘጋጅቶ ለአባሎችና ለሚመለከታቸው ያደርሳል፤በማህበረሰቡ ዓመታዊ በዓላትም ላይ ለሚገኙ ያደርሳል።

25 6 ለስራው የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶችና በጀቶች ያቀርባል፤ያጠናል፤ሲፈቀድለት በስራ ላይ ያውላል።

25 7 በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚመለከታቸውን ሃላፊዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግ ለአባላት መረጃዎችን ይሰጣል።

25 8 ከአባላት በፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን ይመርጣል፤ ሊ/መንበሩ ሲፈቅድለት ተግባራዊ ያደርጋል።

25 9 ማንኛውም የጽሁፍ፤የኤሌክትሮኒክስ፤የቃለ መጠይቅ መግለጫዎች ሁሉ ከመተላለፋቸው በፊት በሊ/መንበሩ መፈቀድ አለባቸው።ለመፈቀዱም የጽሁፍ ማስረጃ ይይዛል።

25 10 ከኮሚቴዎች ጋር ተባብሮ ይሰራል።

አንቀጽ 26 ሴቶች ወጣቶችና ህጻናት

26 1 በጾታቸው የሚደርሱ ችግሮችን ለመቅረፍና ለማስወገድ ይሰራል።

26 2 በማህበረሰቡ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያበረታታል።

26 3 ባህላቸውን አክባሪ፤ቤተሰባቸውንና ወገናቸውን አፍቃሪ እንዲሆኑ የማበረታቻ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን ያቀናብራል።

26 4 ከህዝብ ግንኙነትና ባህል ኪነ ጥበብ ስነ ጽሑፍ ኮሚቴ ጋር በመመካከር ዕቅዶችን ያወጣል፤ያስፈጽማል።

26 5 በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑትን መርጦ ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ያመቻቻል፤ሽልማት እንዲያገኙ ይጥራል።

26 6 ከስሩ ሶስት ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ ይመሰርታል፤ 2/3 የኮሚቴው አባላት ሴቶች ይሆናሉ።

አንቃጽ 27 የባህል ኪነጥበብና ስነ ጽሑፍ ኮሚቴ

27 1 አባላት የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም የአገራችንን የተለያዩ ባህሎችና ታሪኮች፤ስነ ጽሑፍ ፤ግጥም፤በስዕል በድራማ፤በሙዚቃ ወዘተ እንዲያቀርቡ ያደራጃል፤ካስፈለገም ያወዳድራል ፤እንዲሸለሙም ያደርጋል።

27 2 የኢትዮጵያ ቁጥሮች በአባላትና በልጆቻቸው እንዲታወቁ ይጥራል፤ በተወከለበት ስራ ላይም ተግባራዊ በማድረግ እየተረሳ ያለውን ቁጥሮቻችን የመታደግ ሃላፊነትን ይወጣል።

27 3 በዓመት ውስጥ ሊያዘጋጃቸው የታሰቡ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ሃሳብ ያቀርባል፤ ሲፈቀድለትም ተግባራዊ ያደርጋል።

27 4 በማህበረሰቡ ዓመታዊ በዓላት ላይ ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቋትን ቅርሶች በመሰብሰብ፤በፊልምና በድምጽ በማቅረብ ያስተዋውቃል።

27 5 በአየርላንድ በሚደረጉ ዓመታዊ የባህል ቀን ከሴቶች ወጣቶችና ህጻናትና ከህዝብ ግንኙነት ኮሚቴዎች ጋር ተባብሮ ማህበረሰቡ እንዲሳተፍ ያደርጋል።

27 6 የአገራችንን ዋና ዋና በዓላት በህብረት የሚዘጋጅበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤ያቅዳል።

27 7 ከስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጋር ተባብሮ ይሰራል።

አንቃጽ 28 የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ

28 1 በጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጡ ሶስት አባላት ይኖሩታል።

28 2 ለእዚህ ኮሚቴ አባልነት የሚመረጡ አባላት ቢያንስ ለሁለት ዓመት አባል የነበሩና የማህበረሰቡን ህጎች ጠንቅቀው የተረዱ መሆን አለባቸው።

28 3 በምርጫው ወቅት ለጉባዔው የኮሚቴዎችንና የተመራጮችን ሃላፊነት በተመለከተ በቂ ማብራሪያ በመስጠት ምርጫው ግልጽ እንዲሆን ያደርጋል።

28 4 ይህ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አገልግሎቱ የሚጀምረው ከማህበረሰቡ ምስረታ በኋላ በማንኛውም ጊዜ ይሆናል።

አንቀጽ 29 አስመራጭ ኮሚቴ

29 1 ምርጫ ለማካሄድ 3/4 አባላት መገኘት ይኖርባቸዋል።

29 2 በሁለተኛው የምርጫ ጥሪ ሙሉ አባላት ባይገኙ ከጠቅላላው አባላት 51 % ከተገኙ ምርጫውን ያካሂዳል።

29 3 ለእያንዳንዱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የምርጫ ቦታ ቢያንስ 2 ሰዎች ለውድድር መቅረብ አለባቸው።ይሁንና በምርጫ ውስጥ ለመግባት ፈቃድ እንደሚያሳዩት ግለሰቦች ቁጥር መብዛት ወይም ማነስ ሁኔታ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ቁጥሩን በተመለከተ ውሳኔ በመስጠት የኮሚቴ ቦታዎች እንዲሟሉ ያደርጋል።የተጠቆሙት ሰዎች ለቦታው ብቁ መሆናቸውን ከልብ በሆነ ሃቀኝነት ያረጋግጣል።

29 4 የተመራጮችን ዝርዝር ካሳወቀ በኋላ ምርጫው በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ ይካሄዳል።

29 5 አስመራጭ ኮሚቴ ምርጫው በትክክል መካሄዱንና የሁሉም ድምጽ በደንብ መቆጠሩን የምርጫውም ውጤት ለአባሎች መገለጹን ያረጋግጣል።

29 6 አስመራጭ ኮሚቴው የተመረጡት አባላት ለተመረጡበት ዓላማ ቃል መግባታቸውን ያረጋግጣል።

አንቃጽ 30 የመምረጥና የመመረጥ መብት

30 1 ለምርጫ የሚቀርብ ማንኛውም ግለሰብ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ማህበረሰቡ ስለ አባልነት ያወጣውን መስፈርት በትክክል የተወጣ መሆን ይኖርበታል።

30 2 የኮሚቴ አባላት ምርጫ ላይ ድምጽ ለመስጠት አንድ አባል ቢያንስ ለስድስት ወር የማህበረሰቡ አባል ሆኖ የቆየ መሆን ይኖርበታል።

30 3 ተመራጮች የማህበረሰቡን መተዳደሪያ ደንብ ጠንቅቀው የሚያውቁ እንዲሆን ይጠበቅባቸዋል።

አንቀጽ 31 የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ

31 1 የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል።ለስብሰባውም ቦርዱ ከስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ጋር ዝግጅት በማድረግና በመወሰን የስብሰባውን ቀንና ሰዓት ቀደም ብሎ ያሳውቃል።ቦርዱ አስቸኳይ ጉዳይ ካጋጠመው የስብሰባውን አጀንዳ ቀድሞ በማሳወቅ ጠቅላላ ስብሰባ በማንኛውም ጊዜ ሊጠራ ይችላል።

31 2 የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ለመጥራት እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን ለማስተላለፍ አመቺ የሆኑትን ዘዴዎች ኢሜይልና የኮሚኒቲውን ድረ ገጽ ከሚያስተዳድረው አካል ጋር በመነጋገር ይጠቀማል።

አንቀጽ 32 አስተያየትና ቅሬታን ስለመግለጽ

32 1 ማንኛውም አባል በተናጠል ወይም ከሌሎች አባላቶች ጋር በጋራ በመሆን የማህበረሰቡን የስራ አፈጻጸም በተመለከተ ቅሬታ ወይም አስተያየት ሲኖረው ወይም የማህበረሰቡ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት አልተወጡም ብሎ ሲያምን ቅሬታውን ለቦርዱ በጽሑፍ የማቅረብ መብት አለው፤የደብዳቤውን ግልባጭም ለስራ አስፈጻሚው ይሰጣል።

32 2 አንድ አባል ወይም ከዚያ በላይ ተመራጮች ከአገልግሎት ቦታቸው መነሳት አለባቸው ብሎ ሲያምን የአባላቱን 10% የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ ጥያቄውን በጽሑፍ ለቦርዱ ማቅረብ ይችላል።ቦርዱም የቀረበለትን ጥያቄ መርምሮ በቂ ምክንያት አለ ብሎ ሲያምን ጉዳዩን ከአማራጭ አስተያየት ጋር ለጠቅላላ ጉባዔው ያቀርባል።እስከዚያም ድረስ እንዳስፈላጊነቱ ጊዜያዊ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል።

አንቀጽ 33 የማህበረሰቡን ህግና ደንብ ስለ ማሻሻል

33 1 የማህበረሰቡ ቦርድ ማሻሻያዎችን እያጠና ለጠቅላላ ጉባዔው ሲያቀርብና ጠቅላላ ጉባዔው ሲያምንበት ብቻ የማህበረሰቡ ህግና ደንብ ይሻሻላል።የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውና ሌሎች ኮሚቴዎች ማሻሻያዎችን በቦርዱ በኩል ማቅረብ ይችላሉ።በተጨማሪም ማንኛውም አባል ከሌሎች አስር አባላት ጋር በጋራ በመሆን ማሻሻያዎችን በቦርዱ በኩል ማቅረብ ይችላል።ውሳኔውም በቦርዱ በኩል ይፈጸማል።

አንቀጽ 34 ማህበረሰቡን ስለ ማፍረስ

34 1 በአንድ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የማህበረሰቡ ህልውና አስፈላጊ ከማይሆንበት ደረጃ ሲደርስ በአየርላንድ የማህበረሰብ ህግ መሰረትና ከጠቅላላው አባላት ቢያንስ 75% የሚሆኑት በሚገኙበት ከጠቅላላ ጉባዔው በሚተላለፍ ውሳኔ መሰረት ማህበረሰቡ ይፈርሳል።

34 2 በንዑስ አንቀጽ 34 1 ማህበረሰቡ ሲፈርስ የማህበረሰቡ ገንዘብ፤ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት ጉባዔው ለሚመርጠው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይከፋፈላል።

አንቀጽ 35 አበልና ሌላ ክፍያ

35 1 የማህበረሰቡን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በማንኛውም ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ አባላት ምንም ዓይነት ደመወዝ ወይም ክፍያ ሊጠይቁ አይችሉም።ሆኖም ግን ከማህበረሰቡ የስራ እንቅስቃሴ የተነሳ ከከተማ ውጪ ለሚደረጉ የጉዞና ሌሎች ወጪዎች እንዳስፈላጊነቱ ቦርዱ በሚያጸድቀው የወጭ ስኬል መሰረት ወጭ ይደረጋል።ከደብሊን ውጪ የሚደረጉ ጉዞዎች በቦርዱ መጽደቅ አለባቸው።

35 2 በደብሊን ውስጥ ለሚደረጉ ጉዞዎችና ሌሎች ጊዜያዊና ጥቃቅን ወጪዎች የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሊቀ መንበር በሚያዘው መሰረት ወጪ ይደረጋል። ጥቃቅን ወጪዎች የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሊቀ መንበር እንግዶችን ለመቀበል ወይም እንዳስፈላጊነቱ መጠነኛ ግብዣ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ወጪዎች ይጨምራል።

አንቀጽ 36 ኃላፊነትና ተጠያቂነት

36 1 በማህበረሰቡ የስራ ድርሻ የሚከናወነው በፈቃደኝነት ቢሆንም በኃላፊነት የተመደቡ ተመራጮች የማህበረሰቡን ህግና ደንብ እንዲሁም በአየርላንድ የማህበረሰብ ህግን ተከትለው የማህበረሰቡን አንድነት በመጠበቅ የመስራት ኃላፊነትና አደራ የተጣለባቸው ሲሆን ተመራጮች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተናጠልም ሆነ በጋራ ለሚያደርሱት ጥፋትና ጉዳት ተጠያቂዎች ናቸው።

36 2 አንድ አባል ወይም ተመራጭ የማህበረሰቡን ስራ እያካሄደ ባለበት ወቅት ለሚከሰቱ ጥፋትና ጉዳት በህግ ተጠያቂ ቢሆን ማህበረሰቡ ሃላፊነት አይወስድም፤ ሆኖም ማህበረሰቡ እንዳስፈላጊነቱ የበጎ ፈቃድ ርዳታ ሊያደርግለት ይችላል።

አንቀጽ 37 የኮሚቴዎች የስራ ዘመን

37 1 የኮሚቴዎች የስራ ዘመን ሶስት ዓመት ነው

37 –2 ማንኛውም የኮሚቴ አባል ከሁለት የአገልግሎት ጊዜ በላይ መመረጥ አይችልም።ነገር ግን በተጨማሪ አንድ የኮሚቴ ዘመንን አልፎ መመረጥ ይችላል።

አንቀጽ 38 መተዳደሪያ ደንቡ የሚሻሻልበት ወይም የሚቀየርበት ሁኔታዎች

38- 1 መተዳደሪያ ደንቡ የሚሻሻልበት ወይም የሚቀየርበት ከቦርዱ አባላት 2/3ኛው ከጠየቁና ጥያቄው ከጠቅላላ ጉባዔ 2/3ኛው ከደገፈው ብቻ ነው።

አንቀጽ 39 መተዳደሪያ ደንብ የሚጸናበት ጊዜ

አን39 _ 1 ይህ መተዳደሪያ ደንብ ከዛሬ ጥር ሰባት ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል።

 

Comments are closed.